Categories
Categories
Authors
Authors
- Home
- Language/Linguistics
- Language and Identity in Ethiopia, Vol. 2/ቋንቋ እና ነገድ በኢትዮጵያ (ቅፅ ሁለት) by Girma A Demeke
Language and Identity in Ethiopia, Vol. 2/ቋንቋ እና ነገድ በኢትዮጵያ (ቅፅ ሁለት) by Girma A Demeke
Product Description
ይህ መፅሀፍ ከዚህ በፊት ቋንቋ እና ነገድ በኢትዮጵያ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነት እና ቅድመታሪክ በሚል የታተመው ተከታይ ቅፅ ነው። በእዚህ መፅሀፍ፣ ማ. ቅፅ ሁለት፣ የተዳሰሱት የኦሞአዊ፣ የአባይሰሀራዊ እና ምድብ ያልለየላቸው እና/ወይም ንጥል/ብቸኛ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የሚነገሩ ቋንቋዎች እና ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የእነዚህ ተናጋሪዎች ናቸው። መፅሀፉ በእነዚህ ቋንቋዎች እና ተናጋሪዎቻቸው ላይ መሰረታዊ መረጃ ይሰጣል።
ኦሞአዊ በአፍሮኤሽያዊ ስር ከሚገኙት ቤተሰቦች ሁሉ አነስተኛ የጋራ ባህርያት የሚያሳይ ነው። ይህ ባህርይው በሁለት መንገድ ሲተረጎም ይስተዋላል። አንደኛው፣ ኦሞአዊ ከልዕለ-አፍሮኤስያዊ ቀድሞ የተገነጠለ ነው የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ጨርሶውንም የአፍሮኤሽያዊ አባል ተደርጎ መወሰድ አይገባም የሚል ነው። ኦሞአዊ ምንም እንኳ የሚያንፀባርቀው የአፍሮኤሽያዊ ባህርያት አናሳ ቢሆኑም፣ የአፍሮኤሽያዊ ወገን መሆኑን የሚያሳዩ የስነምዕላድ እና የቃላት አስረጅዎች አሉ።
አባይሰሀራዊ እንደአንድ የቋንቋ ዘር ቡድን መውሰዱ ላይ አጥጋቢ መረጃ የለም። ይህ አባባል በኢትዮጵያ የሚገኙትንም የሚመለከት ነው። ለምሳሌ፣ በአባያዊ እና በሱርማዊ ቡድኖችም ሆነ በሌሎቹ፣ ኩናማ፣ ናራ (ኤርትራ)፣ ጉምዝ መሀከል ያለው ግንኙነት የዘር ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ሆኖም በእያንዳንዳቸው ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ተደርጎ ወደፊት የተሻለ መረጃ እስከሚገኝ ድረስ፣ በእዚህ መፅሀፍ የተዳሰሱት በአባይሰሀራዊ ስር ተካተው ነው።
በእዚህ መፅሀፍ ምድብ ያልለየላቸው እና/ወይም ንጥል/ብቸኛ ቋንቋዎች ስር የተዳሰሱት ጫቡ/ሻቡ፣ ዖንጎታ፣ እና የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ናቸው። ጫቡ እና ዖንጎታ ከአፍሮኤሽያዊም ሆነ ከአባይሰሀራዊ ቋንቋዎች ያልሆኑ ባህርያት አሏቸው። ሆኖም በእዚህ ስራ የመጀመሪያው ንጥል/ብቸኛ፣ ሁለተኛው ደግሞ ምድቡ ያልለየ በሚል ቀርበዋል።
***************************
“ዶ/ር ግርማ አውግቸው በሥነ-ቋንቋ ምርምር ላይ የተመሠረቱ የኢትዮጵያን/የአፍሪካ-ቀንድንና የመካካለኛው ምሥራቅን ቋንቋዎች የተመለከቱ ምርጥ መጻሕፍት በመድረስ ሲያቀርቡልን ቆይተዋል። አሁንም ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ በተሰኘ የምርምር ርዕሰ-ጉዳይ የደረሱበትን ውጤት በሀገርኛ ቋንቋ በአራት ቅጽ እያዘጋጁ ይገኛሉ። ቅጽ 1 ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ፤ ቅጽ 2 ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ ለህትመት አብቅተዋል። ቅጽ ሁለት ከኦሞአዊ እና አባይሰሃራዊ ቋንቋዎች በተጨማሪ ብቸኛ ቋንቋዎችን፣ የምልክት ቋንቋዎችን፣ እና አባሪዎችን ያካተተ ግሩም ሥራ ነው። ዶ/ር ግርማ በእነዚህ ርዕሰ-ጉዳዮች ላለፉት አምሳና ስድሳ ዓመታት በዘርፉ የተደረጉትን ምርምሮች በሚያስደንቅ ምሉዕነት ጥንቅቅ አድርገው አቅርበውልናል። ይህን መጽሐፍ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የታሪክ ተማሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንና ተማሪዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ሰዎች፣ እና የኢትዮጵያን ጉዳይ ጉዳዬ የሚሉ ሁሉ ሊያነቡት ይገባል። መፅሀፉ በየትምህርት ተቋማትና በቤተ መጻሕፍት ለምርምርና ለማመሳከሪያነት ሊኖር የሚገባ ዓይነተኛ ስራ ነው።”
—ዳንኤል አበራ፣ የስነ-ልሳን ተመራማሪና በካንአፍሪክ መልታይሜዲያ ኮሚኒኬሽንስ የምርምር ዳይሬክተር
ግርማ አውግቸው ደመቀ የስነልሳን እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ባለሙያ ናቸው። የምርምር ትኩረታቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ታሪክ እና ስነመዋቅር ላይ ነው። በቅርቡ በእንግሊዝኛ ካሳተሟቸው መፅሀፎች መሀከል የአማርኛ ጥንተ አመጣጥ—ሁለተኛ እትም (2013)፣ ሰዋስዋዊ ለውጥ በሴሜቲክ—የአማርኛ ሰዋስው በዘመን ሂደት (2014)፣ እና የአርጎባ ንግግር አይነቶች/ቋንቋዎች (2015) ይገኙባቸዋል።
Historical Linguistics, History, Ethiopia/AFRICA
Trim size: 5.5 x 8.5 inches
Page count: 298